ለዘመን ባንክ አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ጥቆማና የምርጫ ሂደት መስፈርቶችን ለማሳወቅ የወጣ ማስታወቂያ

ዘመን ባንክ አ.ማ. ማክሰኞ መስከረም 26 ቀን 2019 ዓ.ም በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ሴንተር ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት ጀምሮ በሚያካሂደው 18ኛ የባለአክሲዮኖች መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ባንኩን ለቀጣይ ሦስት ዓመታት የሚያስተዳደሩ 12 አባላት የሚኖሩት የዳይሬክተሮች ቦርድ ምርጫን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የኩባንያ አስተዳደር መመሪያ ቁጥር SBB/91/2024 መሰረት ያካሂዳል፡፡ ስለሆነም ለዳይሬክተሮች ቦርድ አባልነት እጩ ሆነው መቅረብና መመረጥ የሚችሉት የሚከተሉትን መስፈርቶች ማሟላት የሚገባቸው መሆኑን ባንኩ በአክብሮት ያስታውቃል፡፡

1. በሁሉም ባለአክሲዮኖች ለሚጠቆሙና ለሚመረጡ ዕጩ የቦርድ ዳይሬክተሮች ማሟላት ያለባቸው መስፈርቶች

1.ቢያንስ ለሁለት ዓመት የባንኩ ባለአክሲዮን የነበረ/ች፤

2.የባንኩ ቦርድ አባል ሆኖ ለመሥራት ፈቃደኛ የሆነ/ች እና ሐላፊነቱ/ቷን በአግባቡ ለመወጣት በቂ ጊዜ ያለው/ያላት፤

3.የሌላ ማንኛውም ባንክ ሠራተኛ ያልሆነ/ች፤

4.ቢያንስ የመጀመሪያ ዲግሪ ያለው/ያላት ወይም ከከፍተኛ የትምህርት ተቋም ተመጣጣኝ የትምህርት ደረጃ እውቅና ያገኘ/ች፤

5.በባንኪንግ፣ በፋይናንስ፣ በሪስክ ማኔጅመንት፣ በአካውንቲንግ፣ በማኔጅመንት፣ በኢኮኖሚክስ፣ በሕግ፣ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን፣ በኦዲቲንግ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና በተዛማጅ የሙያ ዘርፍ ቢያንስ 7 (ሰባት) ዓመት የሥራ ልምድ ያለው/ያላት፤

6.የሌላ የፋይናንስ ተቋም የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ያልሆነ/ች፤

7.በሌሎች ከአራት በበለጡ ተቋማት ውስጥ የቦርድ አባል በመሆን በማገልገል ላይ የማይገኝ/ትገኝ፤

8.በኢትዮጵያም ሆነ ከኢትዮጵያ ውጪ በእምነት ማጉደል ወይም በማጭበርበር ወንጀል ተከሶ/ተከሳ በፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ውሳኔ ያልተሰጠበት/ያልተሰጠባት፤

9.እራሱ/ሷ ወይም እሱ/ሷ በዋና ባለቤትነት የያዘው/ችው ድርጅት ወይም ተፅዕኖ ማሳደር የሚችልበት/የምትችልበት ድርጅት በፍርድ ቤት ወይም አስተዳዳራዊ የዳኝነት ስልጣን ባለው አካል ወይም በመንግስት ተቆጣጣሪ አካላት እምነት በመጣስ ጉዳዩች ላይ ተመርምሮ፣ ታግዶ ወይም ተቀጥቶ የማያውቅ፤

10.እራሱ/ሷ ወይም እሱ/ሷ በዋና ባለቤትነት የያዘው/ችው ድርጅት ወይም ተፅዕኖ ማሳደር የሚችልበት/የምትችልበት ድርጅት ወይም በዳይሬክተርነት ወይም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይም ከፍተኛ ሥራ አስፈፃሚ ወይም ከፍተኛ ባለቤት የሆነበት/ችበት ድርጅት የባንክ ወይም የሌላ ብድር ግዴታውን ወይም የታክስ ክፍያውን ባለመክፈል ተከሶ/ሳ ጥፋተኛ ያልተባለ/ች ወይም ንብረቱ/ቷ በሃራጅ ያልተሸጠበት/ባት፤

11.እራሱ/ሷ ወይም እሱ/ሷ በዋና ባለቤትነት የያዘው/ችው ድርጅት ወይም ተፅዕኖ ማሳደር የሚችልበት/የምትችልበት ድርጅት ወይም በዳይሬክተርነት ወይም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይም ከፍተኛ ሥራ አስፈፃሚ ወይም ከፍተኛ ባለቤት የሆነበት/ችበት ድርጅት ስልጣን ባለው ተቆጣጣሪ የመንግስት አካል የተጠየቀውን/ችውን መረጃ ያልደበቀ/ች፤ የተሳሳተ የፋይናንስ ወይም ሌሎች መግለጫዎች ያላቀረበ/ች ወይም የተቆጣጣሪ አካላት ውሳኔ ላለመቀበል ወይም ላለመገዛት እምቢተኛ ሆኖ የማያውቅ/የማታውቅ፤

12.እራሱ/ሷ ወይም እሱ/ሷ በዋና ባለቤትነት የያዘው/ችው ድርጅት ወይም ተፅዕኖ ማሳደር የሚችልበት/የምትችልበት ድርጅት ወይም በዳይሬክተርነት ወይም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይም ከፍተኛ ሥራ አስፈፃሚ ወይም ከፍተኛ ባለቤት የሆነበት/ችበት ድርጅት በብሔራዊ ባንክ መመሪያ መሰረት ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ከማንኛውም የፋይናንስ ተቋም የተበላሸ የብድር ታሪክ የሌለው፤

13.ባለአክሲዮኑ/ኗ አክሲዮን የገዛበትን/ችበትን ገንዘብ ያገኘው/ችው ከከሰረ ሰው ወይም በአስተዳደር ችግር ምክንያት ኪሳራ ካጋጠመው ሰው ያልሆነ ወይም ገንዘቡን ያገኘው/ችው በማጭበርበር ወይም በህገወጥ መንገድ ያልሆነ፤

14.አግባብነት ባለው የብሔራዊ ባንክ መመሪያ መሰረት በቂ ስንቅ ሳይኖረው/ራት ቼክ በመፃፍ የባንክ ሂሳቡ/ቧ ያልተዘጋበት/ባት፤

15.ባለአክሲዮኑ/ኗ የአክሲዮን ባለቤት በሆነ/ች ጊዜ የነበረው/ራት የሀብት መጠን ከአክሲዮኖቹ ዋጋ በላይ የነበረ፤

16.ሃቀኛ፣ ታማኝ እና መልካም ስም ያለው/ላት፤ በተለይም በማጭበርበር፣ እምነት በማጉደል፣ ትክክለኛ ያልሆነ የሂሳብ መግለጫ በማቅረብና በመሳሰሉት ተከሶ/ሳ በፍ/ቤት የጥፋተኝነት ውሳኔ ተሰጥቶበት/ባት የማያውቅ/ታውቅ፤

17.ከዚህ በፊት በንግድ ማኅበር አደራጅነት፣ ዳይሬክተርነት፣ ሥራ አስኪያጅነት፣ ተቆጣጣሪነት፣ ኦዲተርነት ወይም በሌሎች የአመራር ሐላፊነቶች ላይ ተመድቦ/ባ ሲሰራ/ስትሰራ ከሐላፊነታቸው ጋር በተያያዘ ወይም በማንኛውም ሌላ ሁኔታ በእምነት ማጉደል፣ በስርቆት ወይም ለቦርድ አባልነት ብቁ በማያደርግ ተመሳሳይ ወንጀል ጥፋተኛ ያልተባለ/ች፤

18.በራሱ/ሷ ወይም በሚመራው/በምትመራው ወይም ዳይሬክተር በሆነበት/ችበት ድርጅት ላይ የመክሰር ክስ ያልቀረበበት/ባት ወይም የኪሳራ ውሳኔ ያልተሰጠበት/ባት፣ በኪሳራ ምክንያት ንብረቱ/ቷ ለዕዳ ማቻቻያነት ያልዋለበት/ባት፤

19.የባንክ ብድር ባለመክፈሉ/ሏ ምክንያት ንብረቱ/ቷ በሐራጅ ያልተሸጠ፣ ተከሶ/ሳ ያልተፈረደበት/ያልተፈረደባት ወይም እሱ/ሷ የሚመራው/የምትመራው ወይም ዳይሬክተር የሆነበት/ችበት ድርጅት ከገንዘብ ተቋማት የተበደረውን/ችውን ገንዘብ ባለመክፈሉ ብድሩ ወደ ጤናማ ያልሆነ የብድር ደረጃ ያልዞረበት/ያልገባበት/ባት፤

20.በንግድ ሕግ፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የወጡ መመሪያዎች እና በሌሎች ህጎች ላይ የተገለፁ ሌሎች መስፈርቶች መሟላት አለባቸው፡፡

2. ገለልተኛ ዕጩ የቦርድ ዳይሬክተሮችን በተመለከተ

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያዎች እና በህግ የተቀመጡትን መስፈርቶች የሚያሟሉ ገለልተኛ ዕጩ ዳይሬክተሮች በዳይሬክተሮች ቦርድ ተመልምለው በአስመራጭ ኮሚቴው አማካይነት ለምርጫ ይቀርባሉ፡፡

ማሳሰቢያ

. የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ቁጥር አስራ ሁለት /12/ ሲሆን፤ በገለልተኛ የቦርድ አባልነት አራት /4/ እንዲሁም ገለልተኛ ባልሆኑ የቦርድ አባልነት ስምንት /8/ ዳይሬክተሮች በዕለቱ ይመረጣሉ፤

. ከገለልተኛ ቦርድ አባላት (Independent Directors) ዕጩዎች በስተቀር የሌሎች የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ጥቆማና ምርጫ የሚካሄደው በመደበኛ ጠቅላላ ጉባኤው ዕለት ነው፤

. ዘመን ባንክ አ.ማ ተጽዕኖ ፈጣሪ ባለአክሲዮኖች የሌሉት በመሆኑ ሁሉም የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት በዕለቱ በተገኙት ባለአክሲዮኖች ይመረጣሉ፤

. በዕለቱ አምስት አባላት ያሉት የዳይሬክተሮች ቦርድ ጊዜያዊ አስመራጭ ኮሚቴ በጉባዔው ይመረጣል፤

. የአስመራጭ ኮሚቴ አባላት በቦርድ አባልነት መመረጥ አይችሉም፡፡ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት እና የባንኩ ሠራተኞች የአስመራጭ ኮሚቴው አባል ሆነው መመረጥ አይችሉም፤

. አንድ ባለአክሲዮን ራሱን በእጩነት በመጠቆም በምርጫው ላይ መወዳደር ይችላል፡፡

. ሦስት ዓመት ያገለገሉ ነባር የቦርድ አባላት በድጋሚ መመረጥ ይችላሉ፤

. ከአጠቃላይ የቦርድ አባላት ውስጥ ቢያንስ ሁለት ሴቶች በቦርድ አባልነት መመረጥ አለባቸው፤

. ከማህበሩ ጸሐፊ ውጭ ከባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ እና ከዘርፍ ዋና ሥራ አስፈፃሚዎች (ምክትል ፕሬዝዳንቶች) መካከል ሁለት ሰዎች የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ሆነው ሊመረጡ ይችላሉ።

. የባንኩ ቦርድ አባላት እና የባንኩ ሠራተኞች ባለአክሲዮኖችን ወክለው ድምፅ መስጠት አይችሉም፡፡

. የሚጠቆመው እና የሚመረጠው የቦርድ አባል ድርጅት በሚሆንበት ጊዜ ድርጅቱን በመወከል በቦርድ አባልነት የሚያገለግለው/የምታገለግለው ሰው ማንነት መታወቅ እና ከላይ የተዘረዘሩትን መስፈርቶች የሚያሟላ/የምታሟላ መሆን ይኖርበታል/ባታል፡፡

ማስታወሻ፡ ነሐሴ 26 ቀን 2018 ዓ.ም በታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ ጳጉሜን 1 ቀን 2018 ዓ.ም በታተሙት የሪፖርተር ጋዜጣ አማርኛ እትም፣ ፎርቹን ጋዜጣ እና ካፒታል ጋዜጣ ላይ የዘመን ባንክ አ.ማ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ጥቆማና የምርጫ ሂደት መስፈርቶች ማስታወቂያ የወጣ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁንና በእነዚህ ማስታቂያዎች ላይ “ማሳሳቢያ” በሚለው ክፍል ላይ “ከማህበሩ ጸሐፊ ውጭ ሁለት የባንኩ ሠራተኞች የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ሆነው ሊመረጡ ይችላሉ” ተብሎ የተገለፀ ቢሆንም በ12ኛው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በተሻሻለው የባንኩ መመሰረቻ ጽሑፍ አንቀፅ 20.1.3. ላይ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ሆነው መመረጥ የሚችሉት የባንኩ ሠራተኞች “ከባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ እና ከዘርፍ ዋና ሥራ አስፈፃሚዎች (ምክትል ፕሬዝዳንቶች)” መካከል መሆኑን የሚገልፅ በመሆኑ ይኸው እንዲታወቅ እያሳሰብን፤ ማስታወቂያው በዚህ መልኩ የተሻሻለ መሆኑን በአክብሮት እናሳውቃለን፡፡

ዘመን ባንክ አክሲዮን ማኅበር

Share