የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ እና ዘመን ባንክ የአረንጓዴ የፋይናንስ ሥርዓት ቴክኒካል ድጋፍ ፕሮግራም አጋርነታቸውን ለማጠናከር ተስማሙ፡፡
በመጋቢት 2016 ዓ.ም. በይፋ የተጀመረው ይህ የትብብር ፕሮጀክት የዘመን ባንክን በአየር ንብረትና ተያያዥ የአደጋ አስተዳደርና በአረንጓዴ ፋይናንስ ዘርፍ ያለውን አቅም ለማጠናከር ያለመ ሲሆን ሁለቱም ወገኖች ትብብሩ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

በፕሮግራሙ ማዕቀፍ ዘመን ባንክ በአውሮፓ ኢንቨስትመንት ድጋፍ ከዲኤአይ ግሎባል ጋር በመተባበር በየፋይናንስ ሪፖርት በሁሉም አገሮች ከሚተገበሩ ተመሳሳይ መስፈርቶች አንፃር ያሉ ክፍተቶችንና የአየር ንብረት የአደጋ ተጋላጭነትን ለመለየት የሚያስችሉ የሽግግር ዕቅድ ዝግጅትና የአረንጓዴ ፋይናንስ ስትራቴጂ ማበልፀግን ጨምሮ የተለያዩ ጥናቶችና የአሰልጣኞች ስልጠና ተከናውነዋል፡፡

የማጠናቀቂያ ውይይቱ የዘመን ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር ሰዋለ አባተ ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት፣ ከፍተኛ የሥራ ሐላፊዎች፣ የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ የኢትዮጵያና የአፍሪካ ህብረት ቢሮ ኃላፊ ሌይላ ትራዎሬን ጨምሮ የባንኩና የዲኤአይ ተወካዮች በተገኙበት ግንቦት 12 ቀን 2018 ዓ.ም. ተካሂዷል።
በወቅቱም የትብብሩን ስኬታማነት በማስመልከት ዘመን ባንክ ለአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክና ለዲኤአይ አማካሪዎች የምስጋና የምስክር ወረቀት አበርክቷል።




