የአገራችን የባንክ ሥራ የወደፊት አቅጣጫ ስኬታማ እንዲሆን ዘላቂነት ያለው፣ አካታች የኢኮኖሚ ዕድገትና ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች የሚያገለግል የፋይናንስ ሥርዓት መገንባት እንደሚያስፈልግ ወ/ሮ እንዬ ቢምር፣ የዘመን ባንክ የዲሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አሳሰቡ፡፡
ዘመን ባንክ “የኢኮኖሚ ሊበራላይዜሽንና የኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ የወደፊት አቅጣጫ” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ ባዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ ሰብሳቢዋ ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር ባንኩ ገንቢ፣ ቀዳሚና አመራሩ ጠንካራ የመሪነት ሚናውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ዝግጅቱን በእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት የከፈቱት አቶ ደረጀ ዘበነ፣ የዘመን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ ይህ ውይይት የሀገራችን ኢኮኖሚ ያለበትን ሁኔታና የፖሊሲ ለውጦችን በማጤን ሊመጡ የሚችሉ ዕድሎችንና ስጋቶችን እንዲሁም መከናወን ያለባቸውን ተግባራት አስመልክቶ የጋራ አቅጣጫዎችን ጠቋሚ መንገድ እንዲሆን በማሰብ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ዶ/ር ቴዎድሮስ መኮንን፣ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ተመራማሪ፣ ባደረጉት ገለጻ የሀገራችን ማክሮ ኢኮኖሚ ያለበትን ደረጃ በመረጃ አስደግፈው ያቀረቡ ሲሆን ባንኮች ከኢኮኖሚ አቅጣጫውና ከአዳዲስ ፖሊሲዎች አንጻር የሚኖራቸውን መልካም ዕድልና ተግዳሮች አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በተጨማሪም የሌሎች ሀገሮችን ልምድ በማጣቀስ የሀገራችን ባንኮች ሊቀስሙት የሚገባውን ልምድ አብራርተዋል፡፡
በአቶ ሚሊዮን ክብረት፣ የቢኦዲ ኢትዮጵያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር፣ በተመራውና ሰኔ 5 ቀን 2017 ዓ.ም በተካሄደው በዚህ ውይይት ላይ የብሔራዊ ባንክ ተወካይ፣ የባንኩ ባለአክስዮኖችና የዲሬክተሮች ቦርድ አባላት፣ ኮርፖሬት ደንበኞች፣ ከፍተኛ አመራር አባላት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የፋይናስ ዘርፍ ላይ የሚገኙ ምሁራን ተሳትፈዋል፡፡