ዘመን ባንክ የመረጃ ደህንነት አስተዳደር ሥርዓት (Information Security Management System) የሚሰጠውንነና ዓለም አቀፍ እውቅና ያለውን የISO/IEC 27001:2022 መስፈርት በማሟላት የማረጋገጫ ሰርቲፊኬት አገኘ።

ይህ ዓለም አቀፍ ማረጋገጫ ባንኩ የደንበኞቹን መረጃ አስተማማኝነት ለማረጋገጥ፣ ለሥራው ወሳኝ የሆኑ መረጃዎችን ለመጠበቅና የላቀ የመረጃ ደህንነት ደረጃ ለማስፈን ያለውን ጽኑ ቁርጠኝነት ያሳያል። እንዲሁም ዘመን ባንክ የመረጃ ደህንነት ስጋቶችን በውጤታማነት ለመለየት፣ ለመገምገምና ለማስተዳደር የሚያስችል ጠንካራ የመረጃ ደህንነት አስተዳደር ሥርዓት መዘርጋቱንና በተግባር ማዋሉን ያረጋግጣል። ይህ ሥርዓት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ካላቸው ምርጥ አሠራሮች ጋር ተጣጥሞ የባንኩን የመረጃ ሀብት ምስጢራዊነት፣ ትክክለኛነት፣ ተዓማኒነትና ዝግጁነት ለማረጋገጥ በሁሉም የሥራ ዘርፎቹ የሚያደርገውን ጥረት ያመለክታል።
ዘመን ባንክ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያለውን የISO/IEC 27001:2022 ማረጋገጫን ማግኘቱ የደንበኞችን መተማመን የበለጠ እያጠናከረ፣ የባለድርሻ አካላትን እምነት እያሳደገ፣ የባንኩን መልካም ስም እያጎለበተ እንዲሁም የሕግና የቁጥጥር መስፈርቶችን በሙሉ ለማክበር፣ የሥራ ብቃትን ለማሳደግና ቀጣይነት ያለው መሻሻልን ለማረጋገጥ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል። በተጨማሪም ይህ ሰርተፊኬሽን የባንኩን የዲጂታል ሽግግር ስትራቴጂ የሚያጠናክር ሲሆን፣ የባንኩ የመረጃ ሀብቶች በዓለም አቀፍ ተቀባይነት ባላቸው የመረጃ ደህንነት መስፈርቶች መሠረት በሥርዓትና በአስተማማኝ አሠራር እየተመሩና እየተጠበቁ መሆናቸውን ለደንበኞች፣ ለአጋር ተቋማት እና ለተቆጣጣሪ አካላት የሚያረጋግጥ እምነት ይፈጥራል።
ISO/IEC 27001 የመረጃ ደህንነት አስተዳደር ሥርዓትን ለመዘርጋት፣ ለመተግበር፣ ለማስጠበቅና በቀጣይነት ለማሻሻል የሚያገለግል ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት ያለው መስፈርት ነው። በዚህ መስፈርት የተረጋገጡ ተቋማት የመረጃ ደህንነት ስጋቶችን በብቃት ለማስተዳደርና መረጃዎችን ለመጠበቅ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያላቸውን የቁጥጥር ሥርዓቶችና የአስተዳደር አሠራሮች ተግባራዊ ማድረጋቸውን ያሳያሉ።
ዘመን ባንክ የዲጂታል ባንክ አገልግሎቶቹን ይበልጥ ለማሳደግና ለማጠናከር ጥረት በሚያደርግበት ወቅት፣ ይህ ሰርተፊኬሽን ለደንበኞች፣ ለሠራተኞች፣ ለአጋር ተቋማትና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት አስተማማኝ፣ ዘላቂና በእምነት ላይ የተመሠረቱ የፋይናንስ አገልግሎቶችን ለማቅረብ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያጠናክር ሌላ ጉልህ ምዕራፍ ነው። እንዲሁም ባንኩ በሁሉም የመረጃ አያያዝና ጥበቃ ሂደቶቹ ከፍተኛ የመረጃ ደህንነት መስፈርቶችን በማስጠበቅ፣ የደንበኞቹንና የሌሎች ባለድርሻ አካላትን መረጃ ደህንነት ማረጋገጥ ቀዳሚ ትኩረቱ መሆኑን ያሳያል።




