ዘመን ባንክ የአሰራር ሥርዓቱን ይበልጥ ለማዘመን ከኢትዮጵያ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር በቅርበት እንደሚሰራ ተገለፀ፡፡ ይህ የተገለፀው የዘመን ባንክ ከፍተኛ የሥራ አመራሮች በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የሥራ ጉብኝት በማድረግ ከኢንስቲትዩቱ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመጀመሪያ ውይይት ባካሄዱበት ወቅት ነው፡፡

በዚህ ወቅት ኢንስቲትዩቱ የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ያበለፀጋቸውን የተለያዩ ሥርዓቶችና የሥራ እንቅስቃሴዎቹን በተመለከተ ለዘመን ባንክ አመራሮች ገለፃ ተደርጎላቸዋል፡፡ በተጨማሪም የዘመን ባንክ የሥራ ሐላፊዎች በኢንስቲትዩቱ የሚገኙትን የሮቦቲክስ ወርክሾፕ፣ የምርት ማሳያ ክፍልና የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ስታርትአፕ ማዕከልን ጎብኝተዋል፡፡

አቶ አስራት ታደሰ የዘመን ባንክ የሪቴይል ባንኪንግ ቺፍ ኦፊሰር በኢንስቲትዩቱ ተስፋ ሰጪ ሥራዎች በመሰራት ላይ እንደሚገኙ ገልፀው ባንኩ የአሰራር ሂደቱን ይበልጥ ለማዘመን ከኢንስቲትዩቱ ጋር በቅርበት እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡ በተጨማሪም አቶ አስራት በኢንስቲትዩቱ የታቀፉ ስታርትአፖች ችግር ፈቺና በተለያዩ ዘርፎች በተግባር ላይ ሊውሉ የሚችሉ መፍትሄዎችን እየሰሩ መሆናቸውን ለመታዘብ መቻላቸውን ገልፀዋል፡፡

ዶ/ር ታዬ ግርማ የኢትዮጵያ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ተቋሙ በተለያዩ ዘርፎች ሀገር በቀል የሆኑ የሰው ሠራሽ አስተውሎት መፍትሄዎችን ለማምጣት እያደረገ ያለውን ጥረት አብራርተዋል፡፡ የፋይናንስ ዘርፉን በዘመናዊ አሰራር ለመደገፍም ከባንኩ ጋር በቅርበት ለመስራት በኢንስቲትዩቱ በኩል ከፍተኛ ፍላጎትና ዝግጁነት መኖሩንም በውይይቱ ወቅት አረጋግጠዋል፡፡

