ዘመን ባንክ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን በፋይናንስና በአቅም ግንባታ በመደገፍ አብሮ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ አቶ አዲስ ወልደ ጨርቆስ የዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወካይና የብድር ቺፍ ኦፊሰር አስታወቁ፡፡

አቶ አዲስ ወልደጨርቆስ እንደገለጹት፤ ዘመን ባንክ ከአጋር ኩባንያዎች ጋር በመተባበር በወጪ ንግድ ላይ አተኩረው በቆዳና በግብርና ምርቶች ማቀነባበር ላይ ለተሰማሩ የተለያዩ ኢንተርፕራይዞች የአቅም ግንባታ ስልጠና ከሰጠ በኋላ ለተወሰኑት ብድር እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ አብዛኞቹ ኢንተርፕራይዞች ደግሞ ከባንኩ ጋር በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ ይህን ጥረቱን በማጠናከር ለመጀመሪያ ዙር ለተመረጡ ኢንተርፕራይዞች ሐላፊዎችና አባላት በተዘጋጀው ስልጠና ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎች ጥቅምት 7 ቀን 2019 ዓ.ም አጠናቀዋል፡፡

አቶ አስራት ታደሰ የሪቴይል ባንኪንግ ቺፍ ኦፊሰር በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ ዘመን ባንክ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ለመደገፍ የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡ ዘመን ባንክ በያዝነው በጀት ዓመት 16 የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ለማካሄድና 150 አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ያሳተፉ የኔትወርኪንግ መርሃግብሮች ለማከናወን ተዘጋጅቷል፡፡

በተጨማሪም የፋይናንስ እውቀት ማጎልበት፣ የወጪ ንግድ ዝግጁነት፣ የቢዝነስ ሥራ አመራርና የህግ ተገዢነት ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎች ይሰጣሉ፡፡





