ዘመን ባንክ በ2017/2018 (እ.አ.አ 2025/26) በጀት ዓመት 10.2 ቢሊየን ብር ያልተጣራ ትርፍ ያስመዘገበ ሲሆን አጠቃላይ የሀብቱ መጠን 116 ቢሊየን ብር ደርሷል፡፡
የባንኩ ዓመታዊ የማኔጅመንት ስብሰባ ከሐምሌ 17 እስከ 18 ቀን 2018 ዓ.ም በተካሄደበት ወቅት ወ/ሮ እንዬ ቢምር የዘመን ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ባደረጉት ንግግር፤ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የላቀ ውጤት መገኘቱን ገልጸው፤ ለዚህ ስኬት ለባንኩ የማኔጅመንት አባላትና ሠራተኞች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በዚህ ወቅት አቶ አስራት ታደሰ የዘመን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወካይና የሪቴል ባንኪንግ ቺፍ ኦፊሰር ባስተላለፉት መልዕክት ባለፈው በጀት ዓመት የባንኩ የተከፈለ ካፒታል ከ14 ቢሊየን ብር በላይ፤ አጠቃላይ ገቢው 17.8 ቢሊየን ብር፣ ጠቅላላ ካፒታሉ 26 ቢሊየን ብር መድረሱን አስታውቀው፤ የነበረው አፈጻጸምም በዘርፉ መለኪያ መስፈርቶች ሲታይ ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ዘመን ባንክ በሠራተኞቹ፣ በደንበኞቹና በአጋሮቹ ድጋፍና አጋርነት ሌላ የተሳካ የበጀት ዓመት በማሳለፉም የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የባንኩ የደንበኞች ተቀማጭ ገንዘብ መጠን ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ32 በመቶ አድጎ 85.4 ቢሊየን ብር የደረሰ ሲሆን የውጭ ምንዛሬ ግኝቱ ደግሞ 698 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ሆኗል፡፡ ይህም ባንኩ ውጪያዊ ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶችን በመቋቋም ጠንካራ አቅም እንደገነባ ያመለክታል፡፡ የባንኩ የተከማቸ ብድር መጠን 52.59 ቢሊየን ብር መድረሱም ተገልጿል፡፡ (ከላይ የተገለጹት የፋይናንስ መረጃዎች ከኦዲት በፊት መሆናቸውን እንገልጻለን፡፡)

ዘመን ባንክ ማህበራዊ ሐላፊነቱን ለመወጣት ባደረገው ጥረት በአዲሰ አበባ ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች የፋይናንስ እውቀትን ለማሳደግ የሚያስችል የግንዛቤ ማበልጸጊያ ስልጠና በባንኩ ከፍተኛ ባለሙያዎች ተሰጥቷል፡፡ እንዲሁም ህብረተሰቡን ከፋይናንስ አጭበርባሪዎች ለመጠበቅ ሲባል ባንኩ በተለያዩ ቋንቋዎች በተዘጋጁ አጫጭር የጽሑፍ መልዕክቶች፣ በዲጂታል ሚዲያ፣ በመገናኛ ብዙኃን በሚሰራጩ መልዕክቶችና በኤቲኤም ላይ በሚቀርቡ ማስታወቂያዎች ትምህርታዊ መልዕክቶች ሲያስተላልፍ ቆይቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት ዘመን ባንክ የቅርንጫፎቹን ቁጥር ወደ 142 በማሳደግ በመላው ሀገራችን ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡



