ዘመን ባንክና የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ለኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ የሚውል 40 ሚሊዮን ዩሮ ለማቅረብ ተስማሙ

ዘመን ባንክና የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ – ግሎባል በአውሮፓ ህብረትና የኢትዮጵያ ቢዝነስ ፎረም ወቅት በግብርና ለተሰማሩ ተቋማት የሚውል 40 ሚሊዮን ዩሮ ስምምነት ተፈራርመዋል።

በስምምነቱ መሰረት የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ 20 ሚሊዮን ዩሮ ለዘመን ባንክ የሚያቀርብ ሲሆን፣ ዘመን ባንክ በበኩሉ ተመሳሳይ መጠን ያለው ገንዘብ በኢትዮጵያ ብር ለተጠቃሚዎች ያቀርባል። ይህም ኢንቨስትመንት ባንኩ በኢትዮጵያ ውስጥ ለንግድ ባንክ በቀጥታ የሰጠው የመጀመሪያው ብድር በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል ።

ይህ የፋይናንስ ድጋፍ ዘመን ባንክ በኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ለተሰማሩና ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ ለሚልኩ አነስተኛነና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ብድር ለማቅረብ ያስችለዋል፡፡ ከአጠቃላይ የገንዘብ ድጋፉ 30 በመቶ የሚሆነው የብድር መጠን የአየር ንብረትና የአካባቢ ጥበቃ ላይ ትኩረት ለሚያደርጉ የግብርና ሥራዎች ይመደባል፡፡ በተጨማሪም የስምምነቱ አንዱ አካል የሴቶችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ በመሆኑ፤ ከበጀቱ ቢያንስ 30 በመቶ የሚሆነው በሴቶች ባለቤትነት ሥራ ላይ ላሉ፣ በሴቶች ለሚመሩ ወይም ለሴቶች የሥራ ዕድል ለሚፈጥሩና ምርትና አገልግሎት ላላቸው ድርጅቶች እንዲውል ተለይቷል።

ስምምነቱ ሚያዝያ 12 ቀን 2018 በአውሮፓ ህብረትና በኢትዮጵያ ቢዝነስ ፎረም ወቅት በአቶ አስራት ታደሰ የዘመን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወካይና የሪቴይል ባንኪንግ ቺፍ ኦፊሰር እና ሚስስ ሌይላ ትራኦሬ በኢትዮጵያና በአፍሪካ ህብረት የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ተጠሪ መካከል ሚስተር ጆዜፍ ሲኬላ የአውሮፓ ዓለም አቀፍ የግንኙነቶች ሐላፊ በተገኙበት ተፈርሟል።

Share