የባንኮች ካፒታላይዜሽን፣ ውህደትና የተቋማት ግዢዎችን ለማሳካት ጠንካራ ተቋማዊ አቅምእንደሚያስፈልግተገለፀ

የባንኮች ካፒታላይዜሽን፣ ውህደትና የተቋማት ግዢዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ጠንካራ ተቋማዊ አቅም መፍጠር እንደሚያስፈልግ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ አስታወቁ፡፡

ዘመን ባንክ ይህንን ርዕሰ ጉዳይ አስመልክቶ ሰኔ 4 ቀን 2018 ዓ.ም ባዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ እንደገለፁት፤ ከሌሎች ባንኮች ጋር መዋሃድ ካፒታልን ለማሳደግ፣ ወጪዎችን ለመቀነስ፣ የቴክኖሎጂ አቅምን ለማሳደግና ብሎም ተወዳዳሪና ጠንካራ የፋይናንስ ተቋም ለመፍጠር ይረዳል፡፡ በአንፃሩ ተፎካካሪ ካለመሆን ሊያጋጥሙ የሚችሉ ስጋቶች እንዳሉም ጠቁመዋል፡፡

ፕሮፌሰር አለማየሁ ዘመን ባንክ በዚህ ረገድ “በካፒታል አቅሙ፣ በዲጂታላይዜሽን፣ በመልካም አስተዳደር ብቃት፣ ገፅታውን በመገንባትና ስጋትን በመቋቋም ረገድ ጠንካራ ስትራቴጂያዊ ዝግጁነት አለው” ብለዋል፡፡

በዚህ መርሃ ግብር ላይ ወ/ሮ እንዬ ቢምር የዘመን ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ባስተላለፉት መልዕክት በፓናል ውይይቱ የቀረበው ሙያዊ ትንተናና የተደረገው ውይይት ጠቃሚ እውቀትና ልምድ እንደተገኘበት አውስተዋል፡፡ ይህንን መሰል መርሃ ግብር ወደፊትም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

አቶ ደረጀ ዘበነ የዘመን ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የፓናል ውይይቱ በባንኮች፣ በተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤቶች፣ በባለድርሻ አካላትና በባለአክሲዮኖች መካከል የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር፣ ልምድ ለመለዋወጥና ወደፊት ለሚወሰዱ ስትራቴጂያዊ አቅጣጫዎች ግብዓት ለመስጠት ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የዴቨሎፕመንት ማክሮ ኢኮኖሚክስና የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ ለበርካታ ዓመታት በማክሮ ኢኮኖሚክስ፣ በማክሮ ኢኮኖሜትሪክ ሞዴሊንግና በዓለም አቀፍ ንግድና ዴቨሎፕመንት ፋይናንስ በመምህርነትና በተመራማሪነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡

Share