ዘመን ባንክ በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት ከታክስ በፊት 9.97 ቢሊዮን ብር ጠቅላላ ትርፍ ሲያስመዘግብ፣ አጠቃላይ ሀብቱም በ31.3 በመቶ በማደግ ወደ116 ቢሊዮን ብር ከፍ ብሏል።
የባንኩ የተከፈለ ካፒታል 14.3 ቢሊዮን ብር እና ጠቅላላ ካፒታሉ ወደ 26 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታውቋል። በተጨማሪም፣ በዘርፉ ቁልፍ የአፈጻጸም መለኪያዎች ሲገመገም፣ የባንኩ ውጤቶች በዘርፉ ከሚታዩ ጠንካራ አፈጻጸሞች መካከል ሆኖ ይገኛል።

ዓመታዊውን የዘመን ባንክ ባለአክሲዮኖች ስብሰባ መስከረም 26 ቀን 2019 ዓ.ም ሲካሄድ በንግግራቸው የከፈቱት ወ/ሮ እንዬ ቢምር የዘመን ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ “2018 በጀት ዓመት ለዘመን ባንክ ጠንካራ የፋይናንስ አፈጻጸምና ቀጣይነት ያለው እድገት የተመዘገበበት ዓመት ነበር።
የዘመን ባንክ ባለአክሲዮኖች በአንድ አክሲዮን የሚያገኙት የትርፍ ድርሻም ጠንካራ ሆኖ የቀጠለ ሲሆን የአንድ አክሲዮን ትርፍ ድርሻ (Earnings per Share) 53.9 በመቶ ሆኗል፡፡

እነዚህ ውጤቶች የባንኩን ጠንካራ የሥራ አፈፃፀም፣ የደንበኞቻችንና የባለአክሲዮኖቻችንን እምነት እንዲሁም የሠራተኞቻችንን ቁርጠኝነት ያሳያሉ። በቀጣይም በፈጠራ፣ በደንበኛ ተኮር አገልግሎትና በዘላቂ እሴት ፈጠራ ላይ በመመስረት እድገታችንን በማስቀጠል ለመላው ባለድርሻ አካላትና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ያለንን አስተዋጽኦ የበለጠ እናጠናክራለን።” በማለት የባንኩን ስኬት አብራርተዋል፡፡

በዚህ የባለአክሲዮኖች ስብሰባ ላይ ይህንን ስኬት አስመልክቶ አቶ ደረጀ ዘበነ የዘመን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ባስተላለፉት መልዕክት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ዘመን ባንክ የተከፈለ ካፒታሉ ከ14 ቢሊየን ብር በላይ፤ አጠቃላይ ገቢውም 17.9 ቢሊየን ብር መድረሱና 6.75 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን ገልፀዋል፡፡
ዘመን ባንክ በሠራተኞቹ፣ በደንበኞቹና በአጋሮቹ ድጋፍና አጋርነት የተሳካ የበጀት ዓመት በማሳለፉ የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ ምስጋና አቅርበዋል፡፡




