የዘመን ባንክ ቺፍ ሆልሴል ባንኪን ኦፊሰር አቶ ሚካኤል ፀጋዬ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪን መደገፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለፁ፡፡ አቶ ሚካኤል ይህን የገለፁት በአዲስ አበባ በተካሄደው የአለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ማህበር (አይኤቲኤ) የፎከስ አፍሪካ ኮንፈረንስ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው፡፡

አቶ ሚካኤል በኢትዮጵያ እየተሻሻለ የመጣውን የፋይናንስ ሁኔታና በቀጥታ ለአቪዬሽን ኢንዱስትሪ የሚሰጠውን ዘርፈ ብዙ ጥቅም በተመለከተ ማብራሪያ ያቀረቡ ሲሆን ሰኔ 2016 ዓ.ም የተጀመሩት ሰፊ የማክሮ ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎች በገበያ ላይ የተመሠረተ የምንዛሬ ተመን ፣ ነፃ የውጭ ምንዛሪ ገበያ እና የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ መቋቋምን ጨምሮ ሌሎች የፖሊሲ ለውጦች የበለጠ ነፃ ገበያና ምቹ ኢንቨስትመንትን እንደሚፈጥሩ ተናግረዋል፡፡
አቶ ሚካኤል ጨምረውም ኢትዮጵያ ለሁሉም ክፍት ወደሆነ፣ ተወዳዳሪና ለተገበያዮች ምቹ ገበያ እየተሸጋገረች እንደሆነ ገልፀው የተሻሻለ የውጭ ምንዛሪ ተደራሽነት መኖሩ ለነዳጅ አቅርቦት ፣ ለኪራይና ለጥገና ክፍያዎች አየር መንገዶችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል ።

“እነዚህ ማሻሻያዎች የኢኮኖሚ እድገትን በማጎልበት፣ ኤክስፖርትን በመደገፍ፣ ግልፅነትን በመፍጠር የባለሀብቶችን በራስ መተማመን ያሳድጋሉ” ያሉት አቶ ሚካኤል የኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪን የበለጠ ለመደገፍ በጠንካራና በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ሁለገብ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የመጀመሪያው የሆነው ዘመን ባንክ፣ የአቪዬሽን ዘርፍን ጨምሮ ለኮርፖሬት ደንበኞች በላቀ የደንበኞች አገልግሎት ፣ በላቀ የቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ በንግድ ፋይናንስ፣ በድንበር ተሻጋሪ የክፍያ አገልግሎቶችና ልዩ የግንኙነት ባንኪንግ መስጠቱን ቀጥሏል።




